16/12/2025
ፈተናን ወደ ስኬት የመቀየር ጥበብ
“When the going gets tough, the tough get going” የሚለው የውጭ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ፈተና ስብራት ሳይሆን የስኬት ምንጭ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ማንኛውም ታላቅ ስኬት የሚገኘው አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ ሳይሆን፣ ፈተናን ወደ ዕድል በመለወጥ ጥበብ መሆኑን በግልጽ እንረዳለን።
ፈተና የህይወት ሂደት አካል እንጂ እንቅፋት አለመሆኑንና እንደውም አብዛኛውን ጊዜ ፈተና የስኬት ምንጭ መሆኑን እናያለን፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ጉዞም በትክክል የዚህ ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ፍልስፍና በመከተል በርካታና ግዙፍ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። የፓርቲያችን ስኬት የሚታየው በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራዊና ቀጠናዊ ፈተናዎች ሲደራረቡ እንኳን አይበገሬነትን በማሳየት፣ የለውጥ አጀንዳውን ወደፊት ማስቀጠል በመቻሉ ነው።
ፓርቲያችን የተጋረጡበትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በመቋቋምና በመቀልበስ፣ ለሌሎች አገሮች ጭምር የጽናትና ስኬት ተምሳሌት ሆኖ መታየት ችሏል፡፡
የፓርቲያችንን ጥንካሬ ከሚያሳዩ ቁልፍ መገለጫዎች አንዱ የፀደቀው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ነው። ይህ ዕቅድ "ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግሥት እና ለጠንካራ ሀገር" በሚል መርህ የተመሰረተ ሲሆን፣ የለውጥ ቀጣይነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
ይህ ስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የተሟላ ሉዓላዊነት፣ የፖሊሲ ነጻነትና ሀገራዊ ክብርን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚያሳይ የቁርጠኝነት ማሳያ ነው።
ብልፅግና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጋርጠውበት የነበሩት ከፖለቲካዊ ሴራ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችና ፈተናዎች በአይበገሬነት በመቋቋም ፈተናዎችን ወደ ዕድል የመለወጥ ድንቅ ብቃትን አሳይቷል። ፈተናዎች የብልፅግና ፓርቲን መርሆች የሸረሸሩ ሳይሆን፣ ይልቁንም አይበገሬነቱን ያጎሉ ናቸው። ፓርቲው የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የሀገርን ኢኮኖሚያዊ መሰረት ለማጠናከር በሚያደርገው ጥረት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚመጡ ጫናዎችን በብቃት ተቋቁሟል፣ ይህም የፓርቲያችንን የአስተሳሰብ ብቃትና ብስለት አመላክቷል።
ፓርቲያችን ብልፅግና ፈተናዎችን ወደ ስኬት የመቀየር ጥበብ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ በልማት፣ በዲፕሎማሲ እና በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገብናቸው ስኬቶች የፓርቲያችንን ብቃት የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ የወደፊቷ ኢትዮጵያ በብልፅግና እጅ በርካቶች የሚቀኑባትና ምሳሌ የሚያደርጓት እንደሆነች ከወዲሁ ማየት ይቻላል፡፡