09/01/2026
ከምንነጣጠልበት ይልቅ በርካታ የምንደመርበት ጉዳይ ላይ በማተኮር የጉባ ብስራቶችን መድገም ይገባል ፥አቶ መብራቱ ደሴ
ላፍቶ፡ ጥር 1/2018፦ከምንነጣጠልበት ይልቅ በርካታ የምንደመርበት ጉዳይ ላይ በማተኮር የጉባ ብስራቶችን መድገም ይገባል ሲሉ የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ ገለጹ።
በዛሬው ዕለት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ "የጉባ ብስራቶች የወል ትርክት ትዕምርቶች" በሚል መሪ ቃል 6ተኛው አብርሆት የኪነ-ጥበብ ምሽት በለቡ መብራት ኃይል ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ የክፍለ ከተማው አፈጉባኤ አቶ ወጋየሁ ኃይሉን ጨምሮ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከ13ቱም ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የጥበብ አፍቃሪያን ታድመዋል።
የኪነ- ጥበብ ምሽት መርሃ ግብሩን የክፍለ ከተማው ባህልና ኪነ- ጥበብ ጽ/ቤት ያዘጋጀው ሲሆን የጉባ ብስራቶችን በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም የሚያስችል እንዲሁም ገዢ ትርክትን በስነ ጽሁፍ ስራዎች ለማስረጽ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
በእለቱ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፍት የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አቶ መብራቱ ደሴ፥ከምንነጣጠልበት ይልቅ በርካታ የምንደመርበት ጉዳይ ላይ በማተኮር የጉባ ብስራቶችን መድገም ይገባል ያሉ ሲሆን ወጣቶች ከመታደም ባለፈ በውሳጣቸው ያለውን ተሰጥኦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
አክለውም እኛ ኢትዮጲያውያን ችለን የተገኘንበትን የጉባ ብስራቶች በሌሎች የልማት ስራዎች መድገም ያስፈልጋል ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትልና ፖለቲካ ዘርፉ ኃላፊ አቶ ጎሳ ወርቁ፥ አሰባሳቢ ገዢ የሆነ የወል ትርክት ለመገንባት እኔ ከሚል እኛ ወደሚል እሳቤ በመሻገር ፀጋዎቻችንን በጋራ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የክፍለ ከተማው ባህል ኪነ-ጥበብ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አዲሴ ጌትነት ፥በጉባ ላይ ያሳየነውን አርበኝነት ለመድገም አሰባሳቢ በሆኑ የጋራ ትርክቶችን በኪነ ጥበብ እያዋዛን የምንገልጽበት ምሽት ነው ብለዋል።
በመድረኩ አጭር ተውኔት፣ ግጥም እንዲሁም ሌሎች አዝናኝና አስተማሪ የሆኑ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ለታዳሚያን ቀርቧል።