11/07/2026
የማስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መጠናከር ጤናማ ትውልድ እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚያጎለብት መሆኑን የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።
ኦቢኤን ሣይበር ሚዲያ ሐምሌ 04/2018
በሐረር ከተማ በሚገኘው የአባድር ፕላዛ መናፈሻ ስፍራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄዷል።
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው መርሃ ግብር የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች፣ የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ ህጻናትና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙራድ አብዲ በወቅቱ እንዳሉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአካል ጥንካሬ፣ ለአእምሮ እድገት እንዲሁም ጤናማና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት ስፖርት 'ለሁሉም፣ በሁሉም ስፍራ' በሚል መርህ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከጤና ጥቅሙ ባለፈ የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚያጎለብትና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰል ስፖርታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ በበኩላቸው፤ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የኮሪደር ልማትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል ብለዋል።
በዚህም አደጋ ተደቅኖባቸው የነበሩ ቅርሶችን ለመታደግ ከማስቻሉ ባለፈ፣ ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ይበልጥ ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም፣ በክልሉ መጪው ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም “ሩጫ በህያው ሙዚየም” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ውድድሩ የስፖርት ቱሪዝምን የማስተዋወቂያ አካል መሆኑንም ተናግረዋል። ኢዜአ