04/09/2026
ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል !
በዘይሴ አካባቢ በጽንፈኛ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለው ጥፋት የሰውን ልጅ ሕሊና የሚሰቀቅና አጥንት የሚያደማ ሆኗል።
"ልዩ ወረዳ እናገኛለን" የሚል የፖለቲካ ጥያቄን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኝነት መንገድ የተሰማሩ አካላት እየፈጸሙት ያለው ድርጊት ከሰብአዊነትም ሆነ ከፈጣሪ ሕግ የወጣ የጭካኔ ጥግ ነው።
ታሞ የሚታከምበት የዘይሴ ደንብሌ ጤና ጣቢያ እና የነገ ተስፋ የሆኑ ሕፃናት የሚቀሰሙበት የሀውሻ ትምህርት ቤት በእሳት ጋይተው አመድ ሲሆኑ ማየት ምንኛ ያሳዝናል! የሕዝብን መሠረተ ልማት ማውደም ለማን ይጠቅማል?
በኦጎሌ፣ በበኖ፣ በጋርዜታ፣ በጋልመ፣ ትጎ፣ ማዥ፣ እና ብዥጋዴ መንደሮች ላይ የንጹሐን ዜጎች ቤትና ንብረት ማቃጠል እና ከቀያቸው ማፈናቀል ምን ዓይነት የፖለቲካ ግብ ቢኖር ነው ? ይህ ተንኮል ለምን ይጠቅማችኋል ??
የዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ገዛኸኝ እንዲሁም በዘይሴ ኤልጎ ፈንጎ ሞዴል አርሶ አደርና አስታራቂ የሀገር ሽማግሌ የነበሩት ሸጋ ኃይሌን መግደል የትኛውን የሰላም መንገድ ያሳያል? የንጹሐን ሕይወት እንዲህ በቀላሉ መጥፋቱ እጅግ ልብን ይሰብራል።
በዘይሴ ወዜቃ ቀበሌ የተፈጸመው ድርጊት ግን ከጭካኔም በላይ ሆኖ ለቃላት ይከብዳል። አባታቸውን ተከትለው የወጡ ሁለት ምስኪን ሕፃናትን፣ አባታቸው ለማምለጥ ሲሮጥ እነሱን ይዞ ወደ እሳት መጣል ምን ዓይነት ክፉ መንፈስ ቢሰፍን ነው? እነዚህ ሕፃናት ምን በደሉ? ይህ በፈጣሪም በሰውም ፊት ፈጽሞ የማይረሳ ታላቅ በደል ነው!
የወዘቃ ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ማቃጠልም ሕዝብን ለአገልግሎት እጦት ከመዳረግ ውጭ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።
ይህንን ሁሉ ግፍ የፈጸማችሁ አካላት፤ በንጹሐን ደም፣ በሕፃናት ስቃይና በተቋማት ውድመት ላይ የሚቆም መዋቅር ለማንም የሚጠቅም በረከት የለውም። ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ የሚመጣ መዋቅር የሞቱትን አይመልስም፣ የቆሰለውን ሕሊናም አያክምም።
በኤሌዛ እና ገንዶ ላይ እርስ በርስ መገዳደል ውስጥ መግባታችሁ የፈጣሪ ፍርድ መጀመሩን አያሳይምን? የንጹሐን ደም መሬት ላይ ፈሶ አይቀርም፤ ጊዜው ሲደርስ ፈጣሪ ይጠይቃል!
የገዛ ወገናችሁን መግደል፣ ሕፃናትን ለእሳት መዳረግና የሕዝብን ሀብት ማውደም ለነገው ትውልድ የምታወርሱት ጥቁር ጠባሳ ነው። ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ! ከጥፋት መንገድ ውጡ።
ሰላም የሚገኘው በውይይት እንጂ በደም መፋሰስ አይደለም። የንጹሐን ደም መጮኹን ሳያቆም፣ የፈጣሪ ቁጣ ሳይበረታባችሁ ለሰላም እጃችሁን ስጡ።
በዘይሴ አከባቢ የፈሰሰ የንጹሐን ደም ይጮኻል!
ቀን ይመጣል ፣እግዚአብሔር ይፈርዳል ተመለሱ !